ኢትዮጵያ በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን እንዲዘጋ መወሰኗን አስታወቀች።
By Ashenafi
Oct 1, 20261 min read
ኢትዮጵያ በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን እንዲዘጋ መወሰኗን አስታወቀች። በአዲስ አበባ የሚገኙ 10 ኤርትራውያን ዲፕሎማቶችም በ48 ሰዓት ኢትዮጵያን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥታለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ሐሙስ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ለኤርትራ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ላልሆኑ “ጠብ ጫሪነት” እና “ትንኮሳ” ምላሽ ለመስጠት ነው። ይህን ተከትሎም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ “በኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት ላይ ስጋት በሚደቅኑ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሰማርተዋል” ባላቸው ኤርትራውያን ዲፕሎማቶች ላይ ከሀገር የማባረር እርምጃ ወስዷል።
“የኤርትራ መንግስት በሉዓላዊ ሀገራት መካከል ያሉ ግንኙነቶችን ከሚመሩ መርሆዎች ጋር የሚቃረኑ ማናቸውንም ድርጊቶች እንዲያቆም ኢትዮጵያ ታሳስባለች” ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ላይ አስፍሯል። ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላትን “ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና የህዝብ ለህዝብ ቁርኝት” “ጠንካራ” ሲል የገለጸው የሚኒስቴሩ መግለጫ፤ ሀገሪቱ ለእነዚህ “ከፍተኛ ቦታ የምትሰጥ” መሆኑንም አስገንዝቧል።
ኢትዮጵያ “በሰላም አብሮ ለመኖር፣ ለቀጠናዊ መረጋጋት እና ትስስር” ያለማሰለስ “ቅድሚያ ስትሰጥ” መቆየቷን ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስታውሷል። ሀገሪቱ “አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት”፤ አሁንም ቁርጠኝነቱ ያላት መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በአፍሪካ ቀንድ “ዘላቂ ሰላም፣ ደህንነት እና ቀጠናዊ ትስስር” ለማረጋገጥ፤ ኢትዮጵያ ከሁሉም ሀገራት ጋር እንደምትሰራም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ አስፍሯል።

